የአዲስ አበባ ፖሊስ አርቲስት አንዷለም ጎሳን ከዕጮኛው ሞት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር እንዳዋለው ገለጸ


የአዲስ አበባ ፖሊስ ታዋቂው ድምጻዊ አንዷለም ጎሳን ከዕጮኛው ቀነኒ አዱኛ ሞት ጋር በተያያዝ በቁጥጥር ስር አውሎት ምርመራ እያደረገበት መሆኑን አስታወቀ።

ቀነኒ አዱኛ መጋቢት 01/2017 ዓ.ም. ሌሊት 10 ሰዓት አካባቢ እጮኛዋ ጋር ከሚኖሩበት ሕንጻ 5ኛ ፎቅ በረንዳ ላይ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ መውደቋ ለህልፈቷ ምክንያት መሆኑን ፖሊስ አመልክቷል።

በማኅበራዊ ሚዲያ በርካታ ተከታዮች ያሏት ቀነኒ ሞትን ተከትሎ በርካቶች ሐዘናቸውን ከመግለፅ ባሻገር የሞቷ ምክንያት እንዲጣራ እየጠየቁ ይገኛሉ።

ክስተቱን ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጾ፤ ሟች ቀነኒ አዱኛ "ከበረንዳ ላይ በወደቀችበት ወቅት በቤቱ ውስጥ የነበረውን ባለቤቷን ድምፃዊ አንዷለም ጎሳን በቁጥጥር ስር በማዋል" ምርመራ እያደረገ መሆኑን አሳውቋል።

ፖሊስ የሟች አስከሬን ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል መወሰዱን የገለጸ ሲሆን፣ የአርቲስት አንዷለም ማኔጀር ሌሊሳ ኢንድሪስም ይህንን አረጋግጦ የቀብር ሥነ-ሥርዓቷ ዛሬ ረቡዕ እንደሚከናወን ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግሯል።

ቀነኒ ከሚኖሩበት ሕንጻ መውደቋን እና "ንጋት 11 ሰዓት አካባቢ መሞቷን" ሌሊሳ ተናግሮ አንዷለም እና ቤተሰቦቹ ወድቃ እንዳገኟት አስታውቋል።

ሌሊሳ ንጋት 11 ሰዓት ሰዓት ስልክ ተደውሎ "ቀነኒ ጉዳት ደርሶባት ሆስፒታል እንደገባች" እንደተነገረው ገልጾ፣ "እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ከአምስተኛ ፎቅ ወድቃ ነው የሞተችው። ሁኔታውን ለማጣራት ምርመራ ተጀምሯል" ብሏል።

ማኔጀሩ አክሎም መኖሪያ ቤቱ አዲስ አበባ አራብሳ ሰንሻይን ተብሎ የሚታወቀው አካባቢ መሆኑን ጠቅሶ፣ ጥንዶቹ በሥፍራው ከአንድ ዓመት በላይ መኖራቸውን ተናግሯል።

Post a Comment

0 Comments